በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
“የሰማይ አምላክ ያከናውንልናል፥ እኛም ባሪያዎቹ ተነሥተን እንሠራለን”
(ነህ 2፥20)
“ልጄ ሆይ እራስህን ለእግዚአብሔር ታዘጋጅ ዘንድ ወደ ገዳም ብትሄድ ሰውነትህ ለመከራ አዘጋጅ” (ሲራክ 2፥1)
“ገዳም” የሚለው የግዕዝ ቃል ትርጉም ምድረ በዳ አንድም ዱር ማለት ነው። ጥበበኛው ሰሎሞንም ሲመክር ወደ ገዳም ብትሄድ ሰውነትህን ለመከራ አዘጋጅ አለ ምክንያቱም በገዳም ጾም፣ ጸሎት፣ ሥግደት እና በዲያብሎስ መፈተን ስላለ ነው። ሥርአተ ተባሕትዎ ለባሕታዊያን የጀመረው የአዳም ሰባተኛ ትውልድ የነበረው ሄኖክ፤ ለደናግል ሥርአተ ድንግልናን ጀምሮ የሰጣቸው ቴስብያዊ ኤልያስ መሆኑን ቅዱሳት መጻሕፍት ያስረዳሉ። እንግዲህ በብሕትውና አንድም በምናኔ ከዓለም ወጥቶ፣ ከሰው ተለይቶ ከፍትወተ ሥጋ (ከሥጋ ፍላጎት) ከፍቅረ ንዋይ (ገንዘብ ከመውደድ) ርቀው፤ ጣዕመ ዓለምን ትተው በሕገ መላእክት መኖርን የመረጡ መናንያን በገዳም ቅጠል በጥሰው፣ ዳዋ ጥሰው፣ ጤዛ ልሰው፣ ድንጋይ ተንተርሰው፣ ጸብአ አጋንንትን፣ ግርማ ሌሊትን፣ ድምጸ አራዊትን ታግሰው ለእግዚአብሔር ያላቸውን ጽኑ ፍቅር በዚያ ይሳያሉ። [መናኝ የሚለው ቃል “መነነ” ከሚለው የግዕዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም ዓለምን ተወ አንድም ናቀ ማለት ነው]
በዘመነ ብሉይ እነ ሄኖክ፣ መልከ ጼዴቅ፣ ኤልያስ እና ሌሎች በብሕትውና እና በድንግልና የኖሩ እንደነበረ ሁሉ ይህ ሥርአት በዘመነ ሐዲስም የኤልሳቤጥ እና የዘካሪያስ ልጅ ዮሐንስ መጥምቅም የቀደሙትን አባቶች አብነት በማድረግ ሠላሳ ዘመን በገዳም ተወስኖ እህል ሳይበላ፣ የግመል ጸጉር ለብሶ፣ ወገቡን በጠፍር መታጠቂያ ታጥቆ፣ የማርና የወይን ጠጅ ሳይጠጣ፣ በግብረ ተባሕትዎ ወይም በምናኔ ጸንቶ ኖሯል። “ሕፃኑም አደገ በመንፈስም ጠነከረ፥ ለእስራኤልም እስከ ታየበት ቀን ድረስ በምድረ በዳ (በገዳም) ኖረ።” (ሉቃ 1፥80) (ማቴ 3፥3፤ ማር 1፥2-8፤ ሉቃ 7፥27)
አምላካችን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እድሜው ሠላሳ ዓመት ከሞላው በኋላ በዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠመቀ ከዛም ሳይውል ሳያድር ወዲያው ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ (ቆርንቶስ ምድረ በዳ) ሄደ። (ሉቃ 3፥23፤ ማር 1፥12) እንግዲህ ጌታችን ከአገልግሎቱ ሁሉ በፊት ወደ ገዳም መሄዱን እናስተውል። በእርግጥ በባህሪው እጸድቅ አይል ጻድቅ፤ እከብር አይል ክቡር የሆነ አምላክ ሲሆን ጌታችን ወደ ገዳም የሄደበት ዋና አላማ ገዳምን እና ገዳማዊ ሥርአትን ሊባርክ ነው። አንድም በገዳም ሦስቱን አርእስተ ኃጣውእ (ዋና ኃጢአቶች) ድል ለመንሳት ነው። (ሉቃ 4፥1-13) አንድም ጌታችን ለክርስቲያኖች ሁሉ አብነት ወይም አርአያ ለመሆን በተግባር ሥራን (ጾም፣ ጸሎትና ሥግደት) ሠርቶ ነው እንድንሠራ ያዘዘን። “ኢየሱስም መንፈስ ቅዱስ መልቶበት ከዮርዳኖስ ተመለሰ፥ በመንፈስም ወደ ምድረ በዳ ተመርቶ፥ አርባ ቀን ከዲያብሎስ ተፈተነ። በነዚያም ቀኖች ምንም አልበላም፥ ከተጨረሱም በኋላ ተራበ።” (ሉቃ 4፥1፤ ማቴ 4፥1፤ ማር 1፥13)
የጌታችንን አሰረ ፍኖት (ፈለግ) የተከተለ ከሐዋርያት መካከል ብርሃና ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ እንዲሁ በድንግልና ወይም በምንኩስና በምናኔ ኖሯል። (1ኛ ቆሮ 7፥8) ሐዋርያዊት የሆነችው ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖታችንም ገዳማዊውን ሥርአት ከነቢያት፣ ከሐዋርያት እና ከቀደሙት አባቶቻችን ተቀብላ እስከ ዛሬ ጠብቃ ቆይታለች። በተለይ ገዳማት ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሃይማኖት፣ የቅኔ፣ የዜማ፣ የትርጓሜ፣ የታሪክ እና የፍልስፍና ማስተማሪያ ተቋማት ከመሆን ባሻገር የእርሻ እና የተለያዩ የእደ ጥበብ (የእጅ ሥራ) ውጤቶችን በማቅረብ በማኅበራዊ እና በመጠነ ሃብት (ኢኮኖሚ) እንቅስቃሴ ላይ የጎላ ተሳትፎ ሲያደርጉ ይታያል።
ቅዱስ መጽሐፍ “በአባቶችሽ ፋንታ ልጆች ተወለዱልሽ” (መዝ 45፥16) እንዲል እግዚአብሔር ባነሳሳቸው አባቶችና ምእመናን በሰሜን አሜሪካ በቨርጂንያ ግዛት የሐመረ ብርሃን ቅዱስ አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ገዳም የተመሠረተበት ዋና አላማም ምእመናንን በተለይ ታዳጊ ህጻናትና ወጣት የተዋሕዶ ልጆችን በምግባር እና በሃይማኖት ኮትኩቶ በፈሪሃ እግዚአብሔር ለማሳደግ የሚያስችለውን የአብነት ት/ቤት ለማስፋፋት፣ ተምሮ የማስተማር እንቅስቃሴን ለማጎልበት፣ በአጠቃላይ ቤተ ክርስቲያንን የሚረከብ፤ ሃይማኖቱንና ማንነቱን የተቀበለ ትውልድ ለማፍራት ነው። በመሆኑም ለዚህ መንፈሳዊ ሥራ ማንኛውንም እገዛ በማድረግ አባቶቻችን የተቀበሉትን በረከትና ጸጋ ለመቀበል እንዲችሉ በእግዚአብሔር ስም ጥሪ እናደርጋለን።
“ለእግዚአብሔር የሥራ ጊዜ ነው” (መዝ 119፥126)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!